ትግራይ መቀለ ነው

። ከከተማ አስተዳደሩ ፊት ለፊት ያለ አቧራማ ሜዳ ! ዕነዚህ ዕድሜያቸው ከ13-15 ያልበለጡ ታዳጊዎች የሚያቃጥለው ፀሃይ ደንታ አልሰጣቸውም ። ዐይን የሚያጠፋው አቧራም ግዳቸው አይደለም ። ከቤት በጠዋት ከወጡ ሰዓታት ተቆጥረዋል ። ማታ ሲመሽ ነው የምንገባው አለኝ አንደኛው ልጅ … ና ግባ ተጫወት መሃል ባልገባ ወይስ ምን ይሻልሃል አለኝ ? የሳሳች ካፖርተኒ ኳሷን እያነጠረ ! ኸረ ጋሼ ዋ ልብስህ ይቆሽሻል አለ አንዱ ተከትሎ በአክብሮት ! ገረመኝ ። ልጅነቴ ታወሰኝ ። የጨፌ ቆርቆሮ ሜዳ አቧራማ ሜዳዎች ፈረንሳይ ለጋሲዬን ! እግር ኳስ የትም በምንም ማህበራዊ

ቀውስ ውስጥ በፍቅር የሚተገበረው ዓለምን ያስተሳሰረው ተወዳጅ ጨዋታ ነው ። በዕነዚህ ታዳጊዎች በደስታ ህጉ ተጠብቆ ይተገበራል ። የባርሴሎና አርሰናል ዩናይትድ የተቀዳደዱ መለያዎችን ለብሰዋል ። የእግሮቻቸው ዓውራ ጣቶቻቸው ምቹ ባልሆነው ሜዳ ክፉኛ ተጎድተው ከባዶ እግር ያልተናነሱ ጫማዎች ተጫምተው እግር ኳስን በፍቅር ይጫወታሉ ። ህልማቸው እንደ ሳላዲን ሰይድ አዳነ ግርማ አማኑዔል ገብረ ሚካዔል ሽመልስ በቀለ ጌታነህ ከበደ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መጫወት ነው ። ስፖርት በትግራይ ስሜት ነው ። በፍላጎት በፍቅር በምንም የህይወት ፈተና ውስጥ ይተገበራል ። በጦርነቱ ሰዓት አንጫወትም ነበር ። አሁን ግን እየተጫወትን ነው አለኝ አንደኛው ታዳጊ አቧራ የቃመ ፊቱን እየጠራረገ ! አንተ ሌላ ካለህ ሸራ ጫማህን ትሰጠኛለህ አለኝ ። ቀጠለናም ኳስም የለንም ብትገዛልን ደስ ይለናል አለ ትግሬኛ አማረኛ በቀላቀለ ደስ የሚል ቅላፄ ! ከስንብቴ በፊት የዕነዚህ ልጆች የመጨረሻ ቃል ነው ። ዘር ሀይማኖት ብሄር ፖለቲካ የማይሻው ስፖርት በትግራይ ከጦርነቱ ማግስት ሰፊ ማህበራዊ ቀውስ በፈተነው ክልል ቅንጦት ቢመስልም ገብቶን ከተጠቀምንበት ግን ሀያል አቅም አለው ። ስፖርት ድንብር ተሻጋሪ ዓለምን ያስተሳሰረ ተፅእኖ ፈጣሪ ነው ። የተጣሉትን ያስታረቀ የጦፈ ጦርነት ያስቆመ ማህበራዊ ትስስርን ከፍ ያደረገ የሰላም መሣሪያ ነው ። መቀመጫቸውን በትግራይ አድርገው የክልሉ ዋና የእግር ኳስ ቀለም በመሆን ሀገራቸው ኢትዮጵያን በኢንተርናሽናል መድረክ የወከሉ ኮኮቦችን ያፈሩ ከተደራጀ ህዝባዊ መሠረት ጋር በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተደናቂ የፍክክር መንፈስ ይዘው ይንቀሳቀሱ የነበሩት መቀለ 70 እንደርታ ወልዋሎ አዲግራት ስኹል ሽረ የመሣሠሉ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ዛሬ ሊፈርሱ ገደል አፋፍ ቆመዋል ። ከጦርነቱ ማግስት ከዓመታት በፊት በሚሊየን የሚከፈላቸው የክለቦቹ አንዳንዶቹ ተጨዋቾች በህይወት በልቶ አድሮ ለመኖር መቀለ ሰኞ ገቢያ የቀን ስራ ተባረው እየሰሩ ይገኛሉ ። ወትሮም እንኳን ዘንቦብሽ በሆነው የኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ ስፖርት በትግራይ አሁን በህልውና የመቀጠል ጉዳይ ሆኗል ። በባዶ እግር እነዛ በጠራራ ፀሃይ አቧራ እየቃሙ እግር ኳስን በነፃነት በፍቅር የሚጫወቱ የትግራይ ታዳጊዎች መቀለን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ታወሱኝ ? የህይወት ዕጣፈንታ የሌት ተቀን ፈተናቸው ከእራሴ አወዛገበኝ ። የሰላም ዋጋው ስንት ይሆን ? ብቻ እግር ኳስ ስፖርት በትግራይ ከቀውሱ ማግስትም በፈራረሱ መሠረተ ልማቶች መሃል በፍቅር ይተገበራል ። ህፃናት ታዳጊዎች በመቀለ ከከተማ አሰተዳደሩ ህንፃ ፊት ለፊት ባለ አቧራማ ሜዳ ጨምሮ ከፕላኔት ሆቴል ፊት ለፊት ስቴዲየሙ ጎን ሌት ተቀን ኳስን ተቧድነው ሲጫወቱ አየሁ ። ወደ ትግራይ አቅንተው ፕላኔት ሆቴል መቀለ ካረፉ የዕነዚህ ታዳጊዎች በጩኸት የታጀበ የኳስ ጨዋታ ድባብ ከእንቅልፎዎ በጠዋት ሊቀሰቅስዎ ይችላል ።

ሊከስሙ የተቃረቡ የትግራይ ክልል አውራ ክለቦችን መልሶ በማቋቋም እነዛ ታዳጊዎች የነገ የእነርሱ ባልሆነ ሃጢያት የተፈተነ የህይወት ተስፋን ማለምለም ታሪክም የህይወት ዘላዓለማዊ ስንቅ ንሰሀም ነው ። እናም ውድ ወገኖች በትግራይ ክልል ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ከፍ ያለ መነቃቃት የሚፈጥረው ”ክለቦቻችንን እንታደግ የተሰኘው ታላቅ ማህበራዊ ግብ የሰነቀ ጥሪን በመቀላቀል ሊጠፉ የተቃረቡ ክለቦችን መታደግ ? በበርካታ ማህበራዊ ቀውሶች ውስጥም ሆነው እግር ኳስን በእነዛ ያልተመቸ አቧራማ ሜዳ በፍቅር የሚጫወቱ ነገ እንደ ሳላዲን ሰይድ በዋልያው መለያ ለእናት ሀገራቸው ኢትዮጲያ መጫወት የሚመኙ የትግራይ እልፍ ታዳጊዎችን ህልም ማለምለም ከተዳፈነው ድቅድቅ የህይወት ጨለማም ማውጣት ትውልድ ዛሬም ነገም የሚዘክረው ሀገራዊ የኢትዮጲያዊነት አደራም ነው ። እናም ውድ በሀገር ቤትም ሆነ በመላው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጲያዊያን በቀጣይ ቀናት በመገናኛ ብዙሃን በማህበራዊ ሚዲያው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ውበት ጌጥ የነበሩ የትግራይ ክልል ክለቦችን መልሶ ሟቋቋም ከመፍረስ ለማዳን

” ክለቦቻችን እንታደግ “በሚል መሪ ቃል የተጀመረውን የተደራጀ ማህበራዊ ሚናን ከግቡ ለማድረስ ይፋ የምናደርጋቸው የዘመቻው ፓኬጆችን በመደገፍ ስፖርት ከዘር ከብሄር ከፖለቲካ ከሀይማኖት በፀዳ መልኩ በማረጋገጥ ዘመን የማይረሳው ትውልድ የሚዘክረው ሕያው ታሪክ እንድንሰራ በአክብሮት ጥሪዬን አስተላልፋለሁ ። ምክንያቱም አርሰናል ዩናይትድ ሲቲ ሊቨርፑል ወይ ቼልሲ ማድሪድ ባርሳ እያልን የምንወዳቸው ክለቦች ሌት ተቀንም የምንደግፋቸው እንደ ስሜታችን እንደ ጨዋታ እንቅስቃሴ ውበታቸው የህይወት መዝናኛችን የሆኑ የእግር ኳስ ክለቦች ስለሆኑ እንጂ በብሄራቸው ወይ ፖለቲካዊ አቋማቸው መርጠን አይደለም ። የመቀለ 70 እንደርታ ወልዋሎ ሽረ እና ሌሎች የትግራይ ክለቦች ወቅታዊ ነበራዊ ሐቅም ይህ ነው ።

” ክለቦቻችንን እንታደግ “

ስፖርት ለሰላም ስፖርት ለሀገር አንድነት —

ኤፍሬም የማነ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top