የገረጣው የመቀለው ካምቦሎጆ ለትግራይ ስፖርት ዳግም ወደቆ መነሣት ትንሳዔ በአዲስ ዓመት ተስፋም ስጋትም ” …

ይህ ትናንትን ከዛሬ በዘመን ሂደት ቅብብል ያንፀባረቀ የትግራይ ስቴዲየም ወቅታዊ መልክ ነው ። ከጥልቅ ስፖርታዊ ፍቅር ጋር  በ80ሺህ ደጋፊዎቹ ፊት በጋንታ መቀለ 70 እንደርታ የፕሪሚየር ሊግ የሻምፒዮንነት ድል የደመቀ ማራኪ የመቀለው ካምቦሎጆ በዋንጫዎች ክብር ያሸበረቀ ወርቃማ ትውስታ ነው ። ትናትን ከዛሬ ያመለከተ በፈተናዎች መሃል ከጦርነት ማግስት የገጠመ አሳዛኝ የትግራይ ስቴዲየም ገፅታ ነው ። ከey ንስር ካሜራ ዐይኖች በስተጀርባ ስፖርት በትግራይ ዳግም ከወደቆ መነሣት ተስፋው  ጋር ዛሬም በፈተናዎቹ ውስጥ ከገረጣው የካምቦሎጆ አውድማ በስሜት በፍቅር ይወደዳል ። ከሰፊ  ያልተመለሱ ማህበራዊ ጥያቄ ፈተናዎቹ ተፋጦ እየተጓዘ ባለው ክልል  ስፖርት እግር ኳስ በትግራይ አሁንም ቅንጦት ቢመስልም ሰፊ ዳግም የመነሣት መነቃቃት ስነ ልቦናዊ ጥገና  ከጦርነት ማግስት ለሚያስፈልገው  ማህበረሰብ ግን የነፍስ ሐሴት ማረፊያ ነው ። ጭንቅ መከራን ለመርሳት ብቸኛው በነፃ መድረክ የተገኘ አማራጭ ! በፍቅር የሚወደድ ከጥልቅ ፍላጎት እና ስሜት ጋርም ዕድሜ ፆታ ዘር ሐይማኖት ጎሳ ሳይለይ በሁሉ ማህበረሰብ የሚተገበር … አድማጮች ይህ በጎውን ዓለማ ሰንቀው ከትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ቴክኒካሊ በመተባበር በሽቶ ሚዲያ ባልደረባችን ግደይ አስተባባሪነት የተካሄደው የትግራይ ዋንጫ ስፖርታዊ መድረክ በየአቅጣጫው የተበተኑ የትግራይ የፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ሊግ እና ብሄራዊ ሊግ ተካፋይ ክለቦችን አገናኝቷል ። በጦርነት ግጭት መንፈስ ለማንም ያልጠቀመ በጥፋት ስነ ልቦና የደቀቀው ክልል ማህበረሰብን አቅጣጫን ከጥልቅ የስፖርት መድረክ ፍቅር ፍላጎቱ ጋር የውጤት መሠረት ለማስያዝ ይበል የሚያሰኝ ጅምር መሠረትም ነው ። ምስጋና የሚያንሰው ተደናቂ ተግባር !
” ኤፋችን ” እንደምን አለህ ? ከሚላህ …  ከአራት ዓመት በኋላ ዳግም ስንት መከራ አልፈን ተገናኘን ።  እንዴት ነህ ግን  ወንድማችን እኛ አለን ፈጣሪ ይመስገን … ያኔ 70 እንደርታ  የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ሲሆን  እናንተም ያንን ማራኪ የክለባችን ዶክመንተሪ ፊልም ልትሰሩ ከመጣችሁ አራት ዓመታት በኋላ ደግም  ከብዙ የህይወት ፈተናዎች ጋር ሞትን ተሻግረን  ጓደኞቻችን በየጫካው ጥለን  የትግራይ ዋንጫን ስናሸንፍ ዕዚሁ ሴቴዲየም ዳግም ተገናኘን ። የአምላክ ስራ … ጦርነት ማንን ጠቀመ ? ያውም በወንድም ዓማቾች መሃከል ይኸው ከእኛ ማየት በቂ ነው ። እኛን ተውና ይህ ስቴዲየምን እንኳ ተመልከት ?  እንዴት እንደገረጣ … ሰፊ መሠረተ ልማቶቹ እንዴት እንደፈረሱ … ሁሉ ነገር ዞረህ እንዳየኸው ተበላሽቷል ። ትናንት የምታውቀው ገፅታን እንኳ ለማምጣት ከዕንግዲህ የሚፈጅብን ግዜ …. የወደመ የባከነ የሀገር ወገን ንብረት ነው ።  ሜዳውን ተመልከት ? ጉዳፍ ለተሰንበት ጎይቶቶም የመሣሰሉ እነዛ ሳተና የወርቅ እግሮች የሚፈሱባቸው ሚሊየን ዶላሮችን ያወጡ የመሮጫ ትራኮች ታዘብ ?  መልበሻ ክፍሉ በስቴዲየሙ ዙሪያ የነበሩ መፀዳጃ ቤቶች ሌሎች የተጠናቀቁ መሠረተ ልማቶች እንዴት እንደተበላሹ ማን ይናገርልን ? ማንንስ ተማፅነን ወደ ቀድሞዎ መልካቸው እንመልሳቸው ይሆናል ?  እንጃ በዚህ ሰዐት በክልላችን ሰፊ ሌሎች መንግስት የሚመልሳቸው ማህበራዊ ጥያቄዎች አሉ ? በቀናነት የጀመርከው የትግራይ ክለቦችን የማገዝ የተባረከ ፕሮጀክት ፈጣሪ እንዲያሳካልህ እንመኛለን ። አለን ከጎንህ … በርቱ እኛ ለዚህ Tigray cup  ከአዘጋጆቹ ጋር ሳር በማጨዱ ተባብረን  ሜዳውን እንደ ነገሩ አመቻችተን ከመፍረስ ለመዳን እየታተሩ የሚገኙ  ክለቦችን ወደ ውድድር ተመልሰው  ማየታችን ብቻ  የመጀመሪያ ድላችን ነው ። የመጀመሪያውም በአዲስ ዓመት ያገኘነው ፀጋ በረከታችን ለህዝባችን ። በዚህ የነቃ መንፈስ አዲስ ዓመትም ከ3 ዓመታት በኋላ ልናከብር ነው ። እኛም ከሞት ተርፈን ወንድሞቻችን በየጫካው ጥለን ደግም በስፖርት ሜዳ ክለቦቻችን ለመደገፍ ከመገናኘት በላይ ምን ያስደስታል  አሉኝ በ70 እንደርታ እና ስኹል ሽረ ፍፃሜ ጨዋታ ቀን በትግራይ ስቴዲየም ከአራት ዓመት በኋላ ያገኘዃቸው ጥቂት የስፖርት ቤተሰቦች ….  እንዳትጠራጠር ያ የምታውቀው 80ሺህ ተመልካች በዚህ ስቴዲየም ከማራኪ ድባብ ጋር በቅርብ ቀን እንመልሰዋለን ሲሉ ቃል ገቡልኝ ።  ገረመኝ ። የ70 እንደርታው አቸኖ ወይ አዳነ በሉት አብርሃም ጫምሃይ ፂማሙ የፅናት ተምሳሌት  ጋቱሶ በጦርነቱ ምክንያት ከደረሰበት ምትሃታዊ ጉዳቱ በፈጣሪ ችሮታ አገግሞ አገኘሁት ። በርካታ ሌሎች የትግራይ ስፖርት ዳግም ወድቆ መነሣት ቁልፍ መሠረት ሊሆኑ እየተጉ ያሉ ወገኖች የተለየ ፓሽንን ሲበዛ አደነቅኩ ።
መቀለ ትግራይ ሐውልቲን አሻግር የሚታዘበው ከፕላኔት ሆቴል ፊት ለፊት እንደ በርካታ ቆሞ ቀር በሌሎች የሀገራችን ክልል ከተሞች እንደሚገኙ ወንድሞቹ  ስቴዲየም መሣይ መድረኮች ካልተጠናቀቁ መሠረተ ልማቶቹ ጋር ያለፈ ድንቅ በ80ሺህ ደጋፊዎች ደማቅ ድባብ ያጌጠ ትውስታውን እንደናፈቀ ከጦርነት ማግስት የበለጠ በአሳዛኝ ሁኔታ ለጥገና ዕንኳ በማይበቃ ቅርፅ ተበላሽቶ የቆመው  የትግራይ ስቴዲየምን ሳይ ግን ? አይ የሀገሬ ኢትዮጲያ አዙሪት መች ይሆን የሚያበቃው  አልኩ በውስጤ … የችግር ዐይነቱ መጠን ይለያይ እንጂ ወልዲያ ታወሰችኝ ። ያ 600 ሚሊየን ብር ፈሶበት ባክኖ የቀረ የሼህ መሃመድ ስቴዲየም ! የባህርዳር ሀዋሳ ሲዳማ  ኦሮሚያ ሀረር አፋር እና በዋና ከተማችን አዲስ አበባ ጭምር  እንደ ቅርስ ተገትረው ያሉ ግልጋሎት አልባ እንደ ተቋቋሙ ፈዘው የቀሩ አርማታ ድርድር  የከሸፉ ቢሊዮኖችን የቀረጠፉ የስቴዲየም  ፕሮጀክቶቻችን ታወሱኝ ። ወትሮም አላለልንም እንጂ ዞሮብን ስፖርት ድንበር ተሻጋሪ የሀገር ገፅታ ከፍታን በመልካም ስም የሚገነባ ቱሪዝም ኢኮኖሚን የሚያሳድግ የማህበረሰብ ትውፊት እስቴን ከላቀ የፍክክር አሻራ የሚያሰተሳስር  ማህበራዊ መስተጋብራችንን በነቃ አስተሳሰብ የሚያጎለብት የአንድነታችን መሠረት ቢሆንም ዕርግማን ነው መሠል ለእኛ በመንግሥታት የስርዓት ለውጦች ውስጥ ትናትንም ዛሬም ስፖርት በኢትዮጵያ የትርፍ ግዜ የማያውቁት ወገኖች መቀለጂያ ነው ። እንደ ቅንጦትም የሚታይ ሰፊ ጠቀሜታው የተዘነጋ በዜጎቹ ዘንድ ያለውን ተወዳጅነት የከዳ አማተሮች የከበቡት የአማተሮች መናኸሪያ መጫወቺያም ነው ። መንግስትም በቢሊዮን እንደ ቀልድ ብሮችን እያፈሰሰ ያለ መክሊታቸው በሚሾማቸው ወገኖች የሚመራ መድረክ አድርጎቷል ለሽርፍራፊ ሰከንድ ዕንኳ ዞር ብሎ የማያየው ዘርፍ ነው ስፖርት በኢትዮጵያ ! እናም ጥቅል የሀገሪቱ አዙሪት ፀጋ በረከት ተቋዳሽ የሆነው የትግራይ ክልልም በጦርነት ሳቢያ በገጠመው የህይወት መልክ መቀየር ፈተና ሲታመስ የብዙ ድንቅ የሀገር ስፖርተኞች መፍለቂያ የነበረው የመቀለው ካምቦሎጆ  አውድማ አይሆኑ መንኮታኮትን ለታዘበ ሌላው አሳዛኙ መልክ

ነው ። ፈጣን ግብረ መልስ የሚያስፈልገው የትግራይ ክለቦች ህልውና መሠረት ነው ። ከክለቦቻችን እንታደግ ታላቅ ስፖርታዊ ዓላማ እና ግብን ከሰነቀ 11 የትግራይ ክልል ክለቦችን መልሶ በማቋቋም ዘመቻ ሂደት ሀገራዊ ጥሪ ውስጥ ከእልፍ ደማቅ በደጋፊዎች ድባብ ካሸበረቁ ትውስታዎቹ ጋር በፈተናዎች መሃል የገረጣው የመቀለው ካምቦሎጆን መልሶ መልክ ማስያዝ ሌላው ትውልድ የሚዘክረው ለትግራይ ስፖርት ዳግም ወደቆ መነሣት ትንሳዔ በአዲስ ዓመት ቀአዲስ መንፈስ በአዲስ ተስፋ በፍጥነት መሬት ወርዶ ሊተገበር የሚገባ ቃል ሊሆን ይገባል ።
”  ስፖርት ለሰላም ! ስፖርት ለሀገር አንድነት ! ስፖርት ለሁሉም ለትግራይ ክለቦች ! – ኤፍሬም የማነ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top